ለክርስቲያን ዜና (በምስጋና ሙሉነህ) ፤ ጥቅምት 18 ፤ 2011 ዓ.ም - ጅግጅጋ

ባሳላፍነው ክረምት በሃምሌ ወር በሶማሌ ክልል በተከሰተው ሁከት በጅግጅጋ እና በአካባቢዋ ማለትም በጎዴ፣ ቀብሪበያን፣ በደጋሀቡር፣ በቀብሪደሃር ባሉ ከተሞች ያሉ ክርስቲያኖችን መራራውን ጊዜ አሳልፈዋል። እያሳለፉም ነው። አብዛኛው የሃገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን በአከባቢው በሚገኙ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተክርስቲያናት ላይ የደረሰውን አስከፊ እና አሰቃቂ ጉዳት እና የቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ ሲዘግቡ የወንጌላውያን ክርስቲያኖችን ጉዳይ ግን ቸል ማለታቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በዚህ ገዳይ ላይ ለ ድረ ገጻችን ሰፊ ማብራርያ የሰጡት የጅግጅጋ እና አካባቢው የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብት ሰብሳቢ የሆኑት መጋ ጋሹ ገብረየሱስ በጥቃቱ 5 የወንጌላውያን ክርስትና አማኞች ህይወታቸው እንዳፈ፣ 5 ሴቶች እንደተደፈሩ እና 9 አብያተክርስያናት ንብረታቸውን እንደተዘረፈ ነግረውናል። የተደበደቡት ደግሞ በቁጥር ለማስቀመጥ እስኪከብድ ድረስ ብዙ ናቸው። አማኞች በሌብነት ሳይሆን በጽድቃቸው ላብ ነግደው አመታት ፈጅተው በዕድሜ ያከማቹት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንብረቶቻቸው ወድመዋል፤ተዘርፈዋል። ይህም ብቻ አይደለም፣ በመንገድ ዳር ቺብስ በመጥበስ እና ቡና በማፍላት የሚተዳደሩ ሁሉ ተዘርፈዋል። ከዚህ አስከፊ ሁኔታ ህይወታቸውን ለማትረፍ መኖሪያ ቤታቸውን እንዲሁም የንግድ ተቋማቸውን ባለበት ትተው ለመሰደድ የተገደዱ አማኝ የክርስቶስ ተከታዮች ጥቂት አልበሩም። ስለዚህም ለረሃብ እና ለእንግልት ተዳርገዋል። የክልሉ አብያተ-ክርስትያናት ህብረትም በሌሎች ቦታዎች የሚገኙ ወገኖችን በማስተባበር ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ የተቻለውን ጥረት አድርገዋል።

ጥቃቱ ይዞአቸው የመጣው አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና መንፈሳዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ቃላት የሚገልጹአቸው እንዳልሆኑ መጋቢ ጋሹ አክለው ተናግረዋል። ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ክርስቲያኖች ከትንሽ ነገር ተነስተው በብዙ ጥረት ያመጡትን ሃብት በቀላሉ ሲነጠቁ ኢኮኖሚያቸው እንደተናጋ፤  ከሁከቱ ጋር ተያይዞ በመጣ የጥይት ድምጽ፣ የመኪና ድምጽ እና ዋይታ የተናወጡት ለጋ ህጻናት ትምህርታቸውን መማር እስከማይችሉ ድረስ እስካሁን እንደሚደነግጡ፤ እንደገና ቢከሰትስ የሚል ስጋት ወጥሮ የሚያስጭንቃቸው ብዙ እንደሆኑ ጨምረው ገልጸዋል። በአከባቢው የሚገኙ አማኞች ‹‹እግዚአብሄር ለምን አልጋረደንም? ለምን አላዳነንም?ይሄ ሁሉ ሲሆን የት ነበር?›› በሚል ጥያቄ እንደተዋጡም መጋቢ ጋሹ አልሸሸጉም፡፡

በነሐሴ ወር 2010 አዲሱ የሶማሌ ክልል ፕሬዘደንት ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ቀስ በቀስ እየተመለሱ ሲሆን አንዳንድ ክርስቲያኖች ወደ ቀደሞው ቀያቸው ተመልሰዋል። የወደመባቸውንም የንግድ ተቋም አድሰው ስራቸውን ለመቀጠል ጥረት እያደረጉም ያሉ አሉ። ቤተ፡ ክርስትያናትም መደበኛ ፕሮግሞቻቸውን ማድረግ ጀምረዋል።

እየታዩ ያሉ መልካም ነገሮች ቢኖሩም አሁንም ግን ከተማውን ለቀው ለመውጣት እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ አማኞች ቁጥር ትንሽ የማይባል እንደሆነ ነው የተናገረው። ምክንያቱም ደግሞ ከነበረው አስከፊ ጉዳት የተነሳ ብዙዎች ነገሮች እንደ በፊቱ ይስተካከላሉ የሚል እምነት በማጣታቸው ነው። ይልቁንም ደግሞ እንዳይከሰት በሚል ስጋት ውስጥ ስላሉ ነው። አንጻራዊ የሆነ ሰላም በከተማዎቹ ቢኖርም በወንጌላውያን አማኞች ላይ ከባድ ፍርሃት ጥሎ አልፏል። ከአብያተ-ክርስትያናትም የተዘረፉት ወንበሮች እና መገልገያ ንብረቶች ተመላሽ አልሆኑም። በጅግጅጋ የሚገኙ የአብያተ-ክርስትያናት ህብረት መሪዎች የተዘረፉትን የቤተ-ክርስትያን መገልገያ ንብረቶች ከከተማው አስተዳደር ጋር በመተባባር ለማስመለስ ቢሞክሩም አጥጋቢ ምላሽ አላገኙም።

ይሄን መረጃ የሰጡን ከጅግጅጋ እስከ ጎዴ ያሉት አብያተክርስትያናት ህብረት ሰበሳቢ እንዲሁም የጅግጅጋ 05 ሙሉ ወንጌል መጋቢ የሆኑትን አቶ ጋሹ ገብረየሱስን፣ “እርሶስ ቤተሰቦን ይዘው ከተማውን ለመልቀቅ ያስባሉ?”ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ; - “እንደማንኛውም ሰው እንደዛ ላስብ እችላለሁ፣ ነገር ግን እኔ አገልጋይ ነኝ። የመጨረሻው ሰው ሲወጣ ነው የምወጣው እንጂ የራሴን ነገር አላደርግም። የማላደርገው እግዚአብሄር ለዚህ ህዝብ አስቀምጦኛል ብዬ ስለማምን ነው። እግዚአብሔርን ታምኜ ነው የምኖረው። እግዚአብሔር ነገሮችን እንደሚቀይር አምናለው።” በማለት የእምነት አቋማቸውን ገልጸውልናል።

የሶማሌ ክልል በሃገራችን ከፍተኛው የክርስቲያኖች ስደት እና ስቃይ የሚታይበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ድረገጻችን በጅግጅጋ እና በአካባቢው ለሚገኙ ክርስቲያኖች ሰላም እና መጽናናትን ይመኛል፡፡

 

Pin It

ድረገጻችን በሶማሌ ክልል የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ጉዳይ በየጊዜው እየተከታተለ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡

Comments powered by CComment