ሰኞ ጥቅምት 19 ፤ 2011 ዓም በ ናኦል በፍቃዱ

ሰሞነኛው ወሬ ደግሞ ትጥቅን ስለመፍታት እና ስላለመፍታት ነው፡፡ ከትግል መልስ በሰላም ለመፎካከር ወደ ሃገር ከተመለሱት ፓርቲዎች መካከል የአንደኛው ፓርቲ ሊቀመንበር በቅርቡ በሚድያ ፓርቲያቸው ትጥቁን እንደማይፈታ እና ይህ “sensitive” ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የኢ.ፌ.ዴ..ሪ መንግስትም ለዚህ አጸፋዊ ምላሹን ከማስጠንቀቂያ ጋር መስጠቱን የዜና አውታሮች አሰምተውናል፡፡ ሆኖም አሁንም ከፓርቲው የሚወጡ ዜናዎች ትጥቅ እንደማይፈታ የሚገልጹ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በተለያየ የሃገራችን ክፍል የሚኖሩ ሕዝቦችም ትጥቆቻቸውን እንዳልፈቱ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡

በእርግጥም ትጥቅ መፍታት “sensitive” ጉዳይ ነው፡፡ ትጥቅ ፈቺ ካለ ትጥቅ አስፈቺ የመኖሩ ሁኔታም እንደተባለው በቀላሉ የሚዋጥ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን “sensitive” ጉዳይ እስከመጨረሻው እልባት በመስጠት ደቀመዛሙርቱን ትጥቅ አስፈትቷቸዋል፡፡ እርሱ ትጥቅ አስፈቺ ሆኖ ተከታዮቹ ትጥቃቸውን ፈትተው እንዲከተሉት ግድ ብሏቸዋል፡፡ ክርስቲያን ትጥቁን የፈታ የክርስቶስ ኢየሱስ በጎ ወታደር ነው፡፡

 

          ‹‹ስሙም …. የሰላም ልዑል ይባላል፡፡›› ኢሳ 9፡6 (አ.መ.ት)

 

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንቢት ከተሰጡት ስያሜዎች አንዱ ‹‹የሰላም አለቃ (ልዑል)›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይህም ሊመጣ ያለው መሲህ የሰላም ባለቤት ፣ የሰላም አለቃ ፣ የሰላም ፈጣሪ እና ራሱ ሰላም እንደሆነ ለይሁዳ ሕዝብ በነብዩ ኢሳያስ በኩል የተሰጠ ትልቅ ተስፋ ነበር፡፡

ታዲያ የሮም ግዛት (Roman Empire) ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 27 ዓመተ ዓለም በአውግስጦስ ቄሳር አማካይነት ሲመሰረት ‹‹ፓክስ ሮማና›› ወይም ‹‹ሰላም በሮም ግዛት›› የሚል የ‹ሰላም› ስብከትን ይዞ ነበር፡፡ በ ‹‹ፓክስ ሮማና›› ዘመን የሰላም ልዑል የሆነው የተጠበቀው መሲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ፡፡ እርሱ ከ ‹ፓክስ ሮማና› የሚበልጥ ሰላምን ሰበከ፡፡

የአውግስጦስ ቄሳርን የ‹‹ሰላም›› ስብከት እና የክርስቶስን የሰላም ልዕልና የሚያለያየው ታዲያ አውግስጦስ ቄሳር በጦር እና በጠመንጃ የመጣ ሰላምን ሲሰብክ ክርስቶስ ደግሞ ተከታዮቹን ትጥቅ አስፈትቶ ፣ ዕርቅን ሰብኮ ፣ መስዋዕት ሆኖ ሰላምን የሰበከ የሰላም አራማጅ  የሰላም አብዮተኛ ነበር፡፡

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥም በምድር በኖረበት ጊዜ ሁሉ የሰበከው እና ያስተማረው ደግሞም ደቀ መዛሙርቱን ያዘዘው ሰላማዊ ስለመሆንና ትጥቅን ስለመፍታት ነበር፡፡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት በወንጌላቱ የሰፈሩት ንግግሮቹም ይህንኑ የሚያመላክቱ ናቸው፡-

  • ·‹‹ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ… ቀኝ ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጉንጭህን ደግሞ አዙርለት›› ማቴ 5፡38-39
  • ·‹‹ጠላቶቻችሁን ውደዱ ለሚያሳድደዋችሁም ጸልዩ›› ማቴ 5፡44
  • ·‹‹በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ ፤ ሰይፍን የሚመዙ በሰይፍ ይጠፋሉ፡፡›› ማቴ 26፡52
  • ·‹‹ሰላምን የሚያወርዱ ብጹዓን ናቸው ፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና፡፡›› ማቴ 5፡9

 

                                                                                               ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን ትጥቅ አስፈትቷቸዋል!

 

በ6 ዓ.ም ‹የገሊላው ይሁዳ› የሚባል ግለሰብ የሮማውያንን ቀረጥ በመቃወም በ ሮም ላይ አመጽ አስነስቶ ነበር፡፡ በዚህም ብዙ ተከታዮችን አስታጥቆ ነበርር፡ ይህንን ግለሰብ ሉቃስ በዘገበው በሐዋርያት ስራ መጽሐፍ ፈሪሳዊው ሊቅ ገማልያል እንደጠቀሰው እናነባለን (ሐዋ 5፡37) ፡፡ ‹የገሊላው ይሁዳ› ታሪክ የከሸፈ መሲህነት ታሪክ በመባል ይታወቃል፡፡

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ አውራጃ ናዝሬት በምትባል ከተማ ሲወለድ ከገሊላ ‹የከሸፈው መሲህ› ታሪክ ገና አልበረደም ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል ናትናኤል ‹‹ክርስቶስን /መሲሁን/ አገኘነው›› ሲሉት ‹‹ከናዝሬት መልካም ነገር ይወጣልን?›› (ዩሐ 1፡45-46) ሲል የጠየቀው፡፡ ከገሊላ አውራጃ በእርግጥ የከሸፈው ‹የገሊላው ይሁዳ› መሲህነት ሌላ ሰው ይነሳል ብለው እንዳያስቡ ተስፋ አስቆርጧቸው ነበር፡፡

ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ ከዚያ ክሽፈት ከተወራበት አውራጃ ተወለደ፡፡ የኢየሱስ መንገድ የሚከሽፍ መንገድ አልነበረም፡፡ የኢየሱስ መሲሕነት የሚከሽፍ አልነበረም፡፡ ሐዋርያቱ ኋላ እንደሰበኩትም ኢየሱስ በእርግጥ እርሱ ክርሰቶስ/መሲህ/ ነበር (ሐዋ 5፡42)! ይህ መሲህ ጦር ስላነሳ እና ተከታዮቹን ስላስታጠቀ ሳይሆን ሰላምን ስለሰበከ እና ‹‹ሰይፍህን መልስ›› (ማቴ 26፡52) ብሎ የደቀመዛመርቱን ትጥቅ ስላስፈታ መሲህ ሆኖ አሸንፎ በክብር ታየ!

የሰላሙ ልዑል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ብሔርተኝነት (Jewish Nationalism) ተነሳሽነት ለብዙ ዘመን ከገዚዎቻቸው ጋር ጦር ሲማዘዙ ከነበሩ እና ጥላቻ ሲሰበካቸው ከኖሩ ማሕበረሰብ 12 ሐዋርያትን መረጠ፡፡ ከእርሱ ቀደም እንደነበሩት እንደ የገሊላው ይሁዳ እና ቴዎዳስ (ሐዋ 5፡36-37) ሳይሆን ነገር ግን ተከታዮቹን ሳያስታጥቅ ‹‹ቀኝ ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጉንጭህን ደግሞ አዙርለት›› (ማቴ 5፡38-39) እያለ በፍቅር ዓለምን እንዴት እንደሚማርኩ ተከታዮቹን አስተማረ፡፡

 

                                                                                                 ኢየሱስ ለምን ተከታዩቹን ትጥቅ አስፈታቸው?

 

ፍትሕ በሌለበት እና ክፋት በሞላበት አለም ጌታችን ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን ለምን ትጥቅ እንዲፈቱ እና ሰላማዊ እንዲሆኑ አስገደዳቸው? ብለን መጠየቃችን ትክክል ነው፡፡ በዚህ ዘመን ላለንም ክርስቲያኖች ጌታችን ከዚህ የተለየ ትዕዛዝ የለውም፡፡ ‹‹ትጥቃችሁን ፍቱ! እኔን ምሰሉ!›› እንደሚለን አምናለሁ፡፡ ግን ለምን? ለምንድነው እንዲህ በቃሉ አማካይነት ሰላማውያን እንድንሆንና ከጦር መሳሪያ ራሳችንን እንድናርቅ የሚያስገድደን?

  1. ኢየሱስ ራሱ ሰላም ስለሆነ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን ‹‹ሰላማቻን›› (ኤፌ 2፡14) ደግሞም ‹‹የሰላም ልዑል›› (ኢሳ 9፡6) ይለዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሰን አምኛለሁ ክርስቶስን ተቀብያለሁ የሚል ክርስቲያን ክርስቶስ ሰላም እንደሆነ እንዲያምን ይገደዳል፡፡ ክርስቶስ ሰላም ከሆነ ክርስቶስን መስበክ ሰላምን መስበክ ነው ማለት ነው፡፡ እውነተኛ ሰለም ደግሞ ከትጥቅ ጋር አይሰበክም፡፡ እውነተኛ ሰላም ከፍቅር እና መስዋዕትነት ጋር ነው የሚሰበከው፡፡ ስለዚህም ኢየሱስ ሰላም መሆኑ፡፡ እኛም የሰላም ሰባኪዎች መሆናችን ትጥቃችንን ፈተን እንድንከተለው ያስገድደናል፡፡
  2. ኢየሱስ ራሱ ሰላማዊ ስለሆነ፡-  ጌታችን ኢየሱስ ‹‹ሰላም›› ብቻ ሳይሆን ሰላማዊም ነበር፡፡ እንቅስቃሴውም ሆነ አስተምህሮው ፍጹም ሰላማዊ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ እንቅሰቃሴው አንድም ጊዜ የሕዝብን ሰላም በጠመንጃ ሲያውክ አንመለከተውም፡፡ በንግግሩም ለጦርነት የሚያነሳሳ ንግግርን ሲያደርግ አናየውም፡፡ ስብከቱም ኑሮውም የሚናገረው ኢየሱስ ሰላማዊ እንደሆነ ነው፡፡ ስብከቱ ‹‹ጠላቶቻችሁን ውደዱ›› ተግባሩም ለተፉበት አና ለሰቀሉት ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› እያለ እንጂ ሰይፍን እያማዘዘ አልነበረም፡፡ ክርሰቲያን ዛሬ ሰላማዊ መሆን አለበት ደግሞም ትጥቁን መፍታት አለበት ምክንያቱም ክርስቶስ ሰላማዊ ስለነበር፡፡
  3. በቀል የእግዚአብሔር ስለሆነ፡- ሰላማዊነት ከመስዋእትነት ጋር እንደሚመጣ የታወቀ ነው፡፡ የክርስቶስ ሰላማዊ አካሄድ መስቀል ነው ያተረፈለት፡፡ የቅዱሳን ሐዋርያቱ ሰላማዊ አካሄድ ሰማዕትነት ነው ያስገኘላቸው፡፡ ለጊዜው በእርግጥ የተሸነፉ ይመስላል ነገር ግን ክርስቶስም ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል ደግሞም የወጉት እያዩ ዳግም ይመለሳል፡፡ ደቀመዛሙርቱም በሰማዕትነት ደማቸው እኛን አስገኝተዋል፡፡ ፍሬያቸው በዝቷል፡፡ በመጨረሻው ቀን እግዚአብሔር ስለነሱ ይበቀልላቸዋል (ራዕ 15፡4-6)፡፡
  4. የኢየሱስ መንገድ አሸናፊ ስለሆነ፡- አርስታይደስ የተባለ የሁለተኛው ክፍለዘመን ክርስቲያን በዚያ ዘመን ስለነበሩት  ክርስቲያኖች ሲናገር “ክርስቲያኖች ራሳቸው ላይ እንዲደረግባቸው የማይፈልጉትን ነገር ሌሎች ሰዎች ላይ አያደርጉም ነበር፡፡ ጨቋኞቻቸውን ያጽናናሉ ደግሞም ጓደኞቻቸው ያደግርጓቸዋል፡፡ ለጠላቶቻቸውም መልካምን ያደርጋሉ፡፡ ለጨቋኞቻቸው ከሚያሱያቸው ፍቅር የተነሳ ጨጨቋኞቻቸው ክርስቲያን ለመሆን ይገደዳሉ፡፡›› (The Apology of Aristides 15) ክርስትና በመጨረሻም ያለ ጠመንጃ ሮምን አሸንፏል፡፡ የኢየሱስ መንገድ ለጊዜው አይምሰል እንጂ ማሸነፉ አይቀርም፡፡ ትጥቅ ፈትቶ ሰላማዊ አካሄድ መሄድ ለጊዜው ዋጋ ያስከፍል እንጂ በመጨረሻ ግን ድልን መቀዳጀቱ አይቀርም፡፡

 

ፈረንሳያዊው የጦር መሪ ናፖሊዩን ቦናባርቴ በአንድ ወቅት ስለክርስቶስ ሲናገር ‹‹በታላቁ ስክንድሮስ ፣ ቄሳር ፣ ቻርላማኝ እና እኔ ትላልቅ መንግስታትን መስርተናል፡፡ የእኛ ክህሎት ግን በምን ላይ ነበር የተመሰረተው? በሃይል ላይ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መንግስቱን በፍቅር ላይ መሰረተ ፤ በዚህ ሰዓት ሚልዮኖች ስለስሙ ይሞቱለታል!›› ኢየሱስ ሚልዮኖችን ያሸነፈው በፍቅሩ ነው፡፡

 

ብዙዎችን ያስከተቱት እነ አውግስጦስ ቄሳር ፣ ናፖሊዩን ፣ ታላቁ ስክንድሮስ ፣ ቸርላማኝ ወዘተ አልፈዋል፡፡ ትጥቅ አስፈትቶ ሰላምን የሰበከው ኢየሱስ ግን ዛሬም ሰላም ነው፡፡ ዛሬም መንግስቱ ሰላማዊ ነው፡፡ ዛሬም ልጆቹ ሰላማውያን ደግሞም የሰላም ሰባኪያን ናቸው፡፡ ዛሬም ከልቡ ለተከተለው ኢየሱስ ትጠቅ አስፈቺ ነው፡፡ አዎን ለክርሰቲያኖች የትጥቅ ጉዳይ “sensitive” ጉዳይ አይደለም፡፡ ትጥቅ አስፈቺው ኢየሱስ ሲሆን ትጥቅ ፈቺዎቹ ደግሞ ወደው የተከተሉት ክርስቲያኖች ናቸው፡፡

 

Pin It

Pin It

Comments powered by CComment