ቀደም ባሉት ቀናት የፓኪስታናዊቷ ክርስቲያን የዔሽያ ቢቢን ከእስር የመለቀቅ ገዳይ ዘግበን ነበር፡፡ አሁን አሁን እየወጡ ያሉ ዜናዎች እንደሚያሳዩት ደግሞ አክራሪ የሙስሊም ቡድኖች በፓኪስታን ዋና ዋና መንገዶችን በመዝጋት ዔሽያ ቢቢ ነጻ እንድትወጣ የፈረዱት ዳኞች እንዲገደሉ እየጠየቁ ይገኛሉ።

ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ በሞት ፍርድ ተርታ ተሰልፋ ለስምንት አመታት ለብቻዋ የታሰረችው ዔሽያ ቢቢ በፓኪስታኑ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ በነጻ መለቀቋ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ውሳኔው ከተሰማበት ሰዓት አንስቶ እስከዛሬ ድረስ የፓኪስታን ከተሞች እና ዋና ዋና መንገዶቻቸው በአክራሪ እስላማዊ ቡድኖች ተዘግተው ተቃውሞን እያስተናገዱ ይገኛሉ። የፓኪስታን ክርስቲያኖችም ጸሎት እና ምልጃ እንዲደረግላቸው በዓለም ዙሪያ ያሉ ወገኖቻችውን ጠይቀዋል።

እንደ ሮይተርስ ዘገባ ለውሳኔ የቀረቡት ሶስቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ቢቢ ወንጀለኛ እንደሆነች የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ ስለሌለ የሞት ፍርዱን ሽረዋል። ውሳኔው ለህዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ አክራሪው እስላማዊ ቡድን ተህሪክ ለባይክ (Tehreek-e-Labbaik) እና ደጋፊዎቹ ዋና ዋና መንገዶችን በመዝጋት ተቃውሟቸውን እይሰሙ መሆኑን ሮይተርስ ገልጿል። ተቃውሞውም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በእጅጉ አድጎ እስላማባድ እና ላሆሬን ጨምሮ ሌሎች የፓኪስታን ትልልቅ ከተሞችን እንቅስቃሴ አስቁሟል።  የቢቢ መኖሪያ በሆነው ላሆሬ ከተማ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የእስላማዊ ቡድኑ ማለትም ተህሪክ ለባይክ(Tehreek-e-Labbaik) መስራቾች አንዱ የሆነው ሙሃመድ አፍዛል ቃድሪ ለቢቢ ነጻ መውጣት ምክንያት ናቸው ያላቸውን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዋና ዳኛ የሆነውን ሳቂብ ኒሳር እና ሌሎች ሁለት ዳኞች በሞት እንዲቀጡ ጠይቁአል።

እንደ ኦፕን ዶርስ (Open Doors) ጥናት በዓለማችን ክርስቲያን ሆኖ መገኘት እጅግ መከራ ከሆነባቸው አካባቢዎች ፓኪስታን በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

 

Pin It

Comments powered by CComment