Articles - Newsflash

A A A

‹‹አብ እኔን እንደላከኝ…›› ዩሐ 20፡21 (ከናኦል በፍቃዱ አዲሱ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

መልዕክተኛው ሰዎችን ሁሉ ለማዳን የተላከ ነው፡፡ ራሱ መልዕክት ነው ፣ ደግሞም መልዕክትን ይዞ ነው የመጣው፡፡ ራሱ ወንጌል ነው ፤ ደግሞም ወንጌልን ይዞ ነው የመጣው፡፡ ራሱ ሕይወት ነው ፤ ደግሞም ሕይወት እንዲበዛልን ነው የመጣው፡፡ ራሱ መንገድ ነው ፤ ደግሞም አዲስንና ሕያውን መንገድ ሊመርቅልን ነው የመጣው፡፡ ራሱ ደስታ ፣ ሰላም ፣ እረፍት ፣ የዘላለም ሕይወት ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ደግሞ ይዞ ነው የመጣው - መልዕክተኛው፡፡

ላኪ መሆን ሲችል መልዕክተኛ መሆንን መረጠ፡፡ ላኪ ለመሆን መስተካከልን እንደመቃማት አድርጎ አልቆጠረም፡፡ ይልቅስ መልዕክተኛ ሆኖ ሌሎችን ለማዳን ለላኪው ራሱንና ፈቃዱን አሳልፎ ሰጠ፡፡

መልዕክተኛው እንደመልዕክተኛ ሆኖ ነው የመጣው፡፡ ዙፋን አላስፈለገውም ፤ በበረት ተወለደ፡፡ ዳንኪራ አላጀበውም ፤ በበጎች እስትንፋስ ተከበበ ፡፡ አምልኮ እና ስግደት አልበዛለትም ፤ ይልቅስ ጥፊ እና ግርፊያን ብሎም የመስቀል ሞትን ቀመሰ፡፡ እንደ ላኪ እና ባለቤት መምጣት ሲችል እንደመልዐክተኛ ሆኖ መጣ፡፡ 

መልዕክተኛው በሁሉ ነገሩ የተላከለትን ሕዝብ ይመስል ዘንድ ተገባው፡፡ እነርሱ የሚበሉትን በላ፣ እነርሱ የሚጠጡትን ጠጣ፡፡ እነርሱ የሚለብሱትን ለበሰ፣ እነርሱ የሚናገሩትን ቋንቋ ተጠቀመ፡፡ እነርሱ የሚተነፍሱትን አየር ተነፈሰ ፤ እነርሱ ያከበሩትን በአል አከበረ፡፡ እነርሱ ሲስቁ ሳቀ፤ እነርሱ ሲያዝኑ አዘነ፡፡ እነርሱ ሲጫወቱ ተጫወተ ፤ እነርሱ የተማሩትን ተማረ፡፡ በሁሉ ነገር የተላከለትን ሕዝብ መሰለ፡፡

ይህ ብቻም አይደለም መልዕክተኛው ወደ ተገፉት ሄደ፡፡ ማንም ያልቀረባቸውን ቀረበ፡፡ በሰው ዘንድ የተጠሉትንና እንደ ኀጢአተኛ የተቆጠሩትን አስጠግቶ ወዳጆቹ አደረጋቸው፡፡ በጥል የመጡበትን በፍቅር አሸነፈ፡፡ ለጸብ ሲጠብቁት ፤ ከመካከል መሰወርንና ተሸናፊ መምሰልን መረጠ፡፡ የጠሉትን እየወደደ የወደዱትን ደግሞ ይበልጥ አቀረበ፡፡

ለተጠየቀው ጥያቄ ሁሉ መልስ እየሰጠ መልስ ሆነ፡፡ ለታመሙት ፈውስን አደለ፡፡ ለተራቡት ምግብን አበላ፡፡ ያንቀላፉትን ቀሰቀሳቸው ፤ የታወሩትን ብርሃን ሰጣቸው፡፡ እርሱን የሚፈልገው ቢጠፋ እርሱ የጠፉትን ፈለገ፡፡ በምድርዊ ምክንያት ለፈለጉት ሰማያዊ ምግብን አቀረበ፡፡ መልዕክተኛውመልዕክቱን ይዞ መልዕክት ሆኖ መልዕክቱን አስነበበ፡፡

የተላከበት አላማን አልረሳም ይልቅስ በጭንቅ ሰዐት እንኳ የላኪውን ፈቃድ ሊያደርግ ወደደ፡፡ የራሱን ፈቃድ ትቶ ለእውነት እንደሚነዳ በግ ታረደ፡፡ በሞቱም መልዕክቱን ለአለም አስነበበ፡፡

መልዕክተኛው በሞቱ መልዕክት አለምን አዳነ፡፡ በትንሳኤውም ብዙ መልዕክተኞችን ዳግም ወለደ፡፡ መልዕክተኞቹም የእርሱን መልዕክት ይዘው ልክ እንደ መልዕክተኛው ብርሃናቸውን ለአለም እንዲያበሩ የተሾሙ ናቸው፡፡ የሩጫቸውን ጀማሪ እና ፈጻሚ የሆነውን መልዕክተኛ በመመልከት ሩጫውን እንዲጨርሱ የተመረጡ ናቸው፡፡


መልዕክተኛው ፤ ኢየሱስ

መልዕክተኛው ያለ እና የሚኖር ነው፡፡ ስሙ ደንቅ ነው፡፡ የሰላም አለቃም ነው፡፡ ዘላለም የሚያኖር አባትም ነው፡፡ ድንቅ የሆነ መካሪም ነው፡፡ እንደውም አማኑኤል ነው፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር!

ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ስሞች አልተጠራባቸውም፡፡‹‹እግዚአብሔር (ያለ እና የሚኖር) ያድናል›› የሚል ትርጓሜ ባለው ስም ተጠራ፡፡ ‹‹ኢየሱስ››

የመልዕክተኛው መልዕክት

መልዕክተኛው ‹‹የእግዚአብሔር መንግስት ቀርባለችና ንሰሃ ግቡ! ›› በማለት ጀምሮ በመስቀል ላይ በሞት አፋፍ ‹‹ተፈጸመ›› ብሎ መልዕክቱን ጨረሰ፡፡ በሁለቱ ንግግሮች መካከል ብዙ መልዕክትን አስተላልፏል፡፡ ብዙ አስተምሯል፡፡ ብዙ ምሳሌዎችን ተናግሯል፡፡

የመልዕክተኛውም መልዕክት በሁለቱ ንግሮች ይጠቃለላል ‹‹ንሰሃ ግቡ! የእግዚአብሔር መንግስት ቀርባለች›› እና ‹‹ተፈጸመ››፡፡ የመልዕክቱ ይዘትየሰዎችን ኃጢአተኝነት ለራሳቸው ለሰዎች ማስተወስ እናም በመጨረሻ መዳናቸውን መፈጸም ነበር፡፡

ስለዚህም ንስሃንና የመዳንን መፈጸም በተለያየ መልኩ እየሰበከ እና እያሰተማረ አለፈ፡፡

የመልዕክተኛው ተግባር

መልዕክተኛው በተግባሩ ከመስበክ እና ከማስተማር ባለፈ ብዙዎችን ፈወሰን ፤ በዲያብሎስ እስራት ስር የነበሩትን ነጻ አወጣ፡፡ የተላከበትን መንግስት በስልጣንና በሃይል ገለጸ፡፡

በተግባር መሞቱ ብቻ አይደለም ፡፡ ከሞቱ በኋላም መልዕክተኞችን ‹‹እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲያደርጉ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርቴ አድርጓቸው፡፡›› (ማቴ 28፡18-20) ብሎ ላካቸው፡፡መልዕክተኛው የተላከ እና ላኪም ነበር፡፡ ‹‹አብ እኔን እንደላከኝ እኔም እናንተን እልካችላሁ›› (ዩሐ 20፡21)

...

በእርግጥ መልዕክተኛው ዳግም ይመጣል!

መልዕክተኛው እንደ ሞተ አልቀረም ተነስቷል፡፡ እንደተነሳም አልቆየም አርጓል፡፡ እንዳረገም አይቀርም ይመጣል፡፡ ይመጣል ያየቀድሞ መልዕክተኛ አሁን ግን ፈራጅ ሆኖ፡፡

ይመጣል ያ የቀድሞ የፍቅር ሰባኪ አሁን ግን ፍርድን ተሞልቶ፡፡ ይመጣል ያ የሕማም ሰው አሁን ግን በብርሃን ታጅቦ፡፡ ይመጣል ያ የሐጢአተኞች ወዳጅ አሁን ግን በሐጢአተኞች ሊፈርድ፡፡ ይመጣል እንደሄደ አይቀርም፡፡ ይመጣል!

ማን ይሆን መልዕክተኛ እየተነበበ ጊዜው የሚደርስለት? ማን ይሆን ያ መልዕክተኛ እየሰራ ላኪውን የሚገናኝ? ማን ይሆን ያ መልዕክተኛ በመልዕክቱ ብዙዎችን እየታደገ ጌታው የሚያገኘው? ያ በጎ እና ታማኝ ባሪያ ወደ ተዘጋጀለት የእረፍት ቤት ይገባል፡፡

እስቲ ወደ ኋላ ተመልሰን ከመልዕክተኛው ሕይወት እንማር፡፡ ተልዕኮውን በ ‹‹ተፈጸመ›› እንድናገባድድ የእርሱ ጥንካሬ እና ቁርጠኝነት ያስፈልገናል፡፡

የመልዕክተኛው ጥንካሬ

መልዕክተኛው ላኪ አለው፡፡ የሚሄድለት ሕዝብ ነበረው፡፡ እንዲሁም የሚያቀርበው መልዕክት ነበረው፡፡ በሌላ ንግግር መልዕክተኛው መነሻ፣ መድረሻ እንዲሁም የሚያልፍበት መንገድ ነበረው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን የመልዕክተኛውን አስደናቂ ጉዞ እንዴት እንደገለጸው አብረን እንመልከት 

‹‹እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቆጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም አምሳል ተገኝቶ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም ፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከሞት ፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ፡፡›› (ፊሊጵስዮስ 2፡6-8)

ይህን ጥንታዊ እንደሆነ እና እንደውም በመጀመሪያይቱ የአዲስኪዳን ቤተ ክርስቲያን አማኞች ዘንድ በአንደበት ተሸምድዶ አልያም በመዝሙር መልክ በቃል ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር እንደኖረ የሚነገርለትን ሐሳብ ጠቅሶ ሐዋርያው ጳውሎስ አስደናቂውን የመልዕክተኛውን ጉዞ ያስቃኘናል፡፡ በዚህ ላይ ወደኋላ በሰፊው የምንመሰለስበትን የመልዕክተኛውን መነሻ (‹‹እርሱ ግን በባህርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ›› ቁ 6) ፣ የመልዕክተኛው መንገድ (‹‹የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም አምሳል ተገኝቶ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም ፣ ራሱን ዝቅ አደረገ›› ቁ 7-8) እንዲሁም የመልዕክተኛውን መድረሻ (‹‹እስከሞት ፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ፡›› ቁ 8) እናያለን፡፡

...

 

መልዕክተኛው በጌቴሴማኒ ምን ወሰነ?

 

ታዋቂው የፊልም ዳይሬክተር ሜል ጊብሰን ዳይሬክት ያደረገውንና ያዘጋጀውን የጌታ የኢየሱስን የመጨረሻ ጊዜያት በሚያትተው ‹‹ዘ ፓሽን ኦፍ ዘ ክራይስት›› የተሰኘው ፊልምን የተመለከተ ሰው አንድ አስዳናቂ ነገር ሊያስተውል እንደሚችል አስባለሁ፡፡
ፊልሙ ክርስቶሰ በጌቴሰማኒ ተጨንቆ በማሳየት ይጀምራል፡፡ የክርስቶስ የጌቴሴማኒው ትዕይንት እጅግ በጣም ቀልብ የሚስብና ልብ አጠልጣይ እንደሆነ የፊልሙ ባለሙያዎች በመረዳታቸው ይመስለኛል የኢየሱስን ታሪክ ከጌቴሴማኒ ጀምሮ በፊልም መልክ ለመስራት ያሰቡት፡፡

ታዲያ በዚህ ፊልም ላይ የፊልሙ አዘጋጅ ሜል ጊብሰን ጌታ ኢየሱስ በጌቴሴማኒ ተጨንቆ በነበረበት ጊዜ ሰይጣን በዚያ አከባቢ ተገኝቶ እንዲናገር ፈቅዶለት ነበር፡፡ በፊልሙ ላይ እንደሚታየው ጌታ ኢየሱስ በጌቴሴማኒ ለብቻው እየፀለየ በነበረበት ወቅት ሰይጣን ለስለስ ባለ ድምፅ ኢየሱስን ‹‹አንድ ሰው ስለሰው ልጆች ሃጢአት መሞቱ ልክ አይደለም!›› ይለው ጀመር፡፡ ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ እባቡ የሚያወራውን ወሬ ሳይሰማ ‹‹አባት ሆይ የአንተ ፍቃድ ይሁን!›› የሚለውን ፀሎት ሲፀልይ ያሳያል፡፡ ኢየሱስ በሚፀልበት ጊዜ እጅግ በጣም ያልበውና ላቡ ወደ ደምነት ሲቀየር ፊልሙ ያሳየናል፡፡ ይህ ትዕይንት በእርግጥ በዚህ መልኩ በመፀሐፍ ቅዱሳችን አልተፃፈም ነገር ግን ሜል ጊብሰንና ባልደረቦቹ የጌቴሴማኒውን የጭንቅ ሰዓት ለማሳየት ያደረጉት ጥረት አስደንቆኛል፡፡ ስለጌቴሴማኒ ያለንን መረዳት ከፍ እንድናደርግም ይረዳናል፡፡

መልዕክተኛው ጌታ ኢየሱስ ውሳኔው ቀላል አልነበረም፡፡ ውሳኔው የተስፋ መቁረጥ ውሳኔም አልነበረም፡፡ ውሳኔው ከ ‹ጀምርሁ አይቀር ልጨርሰው› አይነት ውሳኔም አልነበረም፡፡ ውሳኔው ከአርያም የጀመረውን ጉዞ አሁንም ቢሆን ‹የአንተ ፈቃድ ይሁን!› በሚል የሚያስቀጥል ነበር፡፡

የመልዕክተኛው ውሳኔው የሚያም ነበር ፡፡ ‹‹የአንተ ፈቃድ ይሁን! ›› የሚል ነበር፡፡ መልዕክተኛው ከአርያም የጀመረውን ጉዞ ፍጻሜው ላይ ለማድረስ የግድ በጌቴሴማኒ ‹‹አባት ሆይ... የአንተ ፈቃድ ይሁን›› ማለት ነበረበት፡፡ የዕብራውያን ፀሐፊ ‹‹… ሸክም የሚሆነብንን ሁሉ፣ በቀላሉም ተብትቦ የሚይዘንን ኀጢአት አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ፡፡የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፡፡ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሶ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ተቀምጧአል›› (ዕብ 12፡1-2) ይለናል፡፡

ልብ እንበል የእምነታችን ጀማሪ የሆነው መልዕክተኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእምነታችን ፈፃሚ ባይሆን ኖሮ ማንን እንመለከት ነበር?የአምነታችን ጀማሪ የሆነው ኢየሱስ ጌቴሴማኒ ላይ ሃሳቡን ቀይሮ ቢሆን ኖሮ ቀድሞውንስ እምነታችን ይጀመር ነበርን?

ዛሬ በክርስቶስ ስራ ደስተኞች ነን፡፡ በጌቴሴማኒ የተሰማው የድል ዜና እንጂ የሽንፈት አልነበረም፡፡ አለም ሁሉ ሊሰማው የተገባ አንድ ዜና አለ… መልዕክተኛው ጌታችን ኢየሱስ ጌቴሴማኒ ላይ ተስፋ አልቆረጠም! ወደኋላ አላፈገፈገም!

ይህ ለሰው ልጆች እንዴት ያለ ደስ የሚል ዜና ይሆን!  በገዛ ምኞቱ ተውጦ እግዚአብሔርን አልፈልግም ላለ ለሰው ዘር እንዴት ያለ ደስ የሚል ዜና ይሆን! ተወዳጆች የእኔ ፣ የአንተ ፣ የአንቺ እና የእርሶ ታሪክ የኢየሱስ ውሳኔ ላይ ተንጠልጥሎ ነበር፡፡ እንደ እውነታው ከሆነ ታሪካችን  የጀመረው በቀራኒዮ በመስቀሉ ግርጌ ሳይሆን በ ጌቴሴማኒ ከውሳኔው በታች ነው፡፡

ምናልባት ይህንን የክርስቶስን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እያነበብህ/ሽ ይሆን? እንግዲያውስ እርፍ የሚያደርገው ዜና… ኢየሱስ በጌቴሴማኒ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ይልቅስ ‹‹የአንተ ፈቃድ ይሁን›› ብሎ ወደ ፊት ፅዋውን ሊጎነጭ ተራመደ፡፡

 

መልዕክተኛው ጌታ ኢየሱስ በጌቴሴማኒ አማራጭ ነበረውን?

መልዕክተኛው አማራጭ ነበረው ወይ? ወይስ አማራጭ ስለላልነበረው ነው ጌቴሴማኒ ላይ ፈቃዱን ለአብ ያስገዛው? አብዛኛውን ጊዜ ከተለያየ ዕምነት ተከታዮች ጋር በሚኖረን ውይይት የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ለመረዳት ከባድ እንዲሆንባቸው ከሚያደርገው ምክንያት አንዱ ‹‹እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ከመምጠቱ በፊት ከሰማይ ሆኖ ማዳን አይችልም ነበርን? ደግሞስ ለምን ሰው መሆን አስፈለገው?›› የሚለው ጥያቄ ነው፡፡

ይህ ጥያቄ በተዘዋዋሪ ‹‹እግዚአብሔር ሌላ አማራጭ አልነበረውም ወይ?›› የሚል ይመስላል፡፡ ቀደም ብለን ካነሳነው ሃሳብ ጋር ተቀራራቢነት አለው፡፡ ጥያቄውን ለመልዕክተኛው ኢየሱስ ለራሱ አድረገን ‹‹በጌቴሴማኒ ያንን ውሳኔ ከመወሰንህ በፊት አማራጮች ነበሩህ ወይ?›› ብለን መጠየቅ እንችላለን፡፡ ይህ ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህም ጌታ ኢየሱስ ጥሩ መልስ ይሰጠናል፡፡ መልዕክተኛው ጌታ ኢየሱስ በእርግጥ በጌቴሴማኒ ምርጫ ነበረው፡፡ 

ኢየሱስ አማራጭ ነበረው!

 

‹‹ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ ለማስነሳት ስልጣን አለኝ›› (ዩሐ 10፡18)

መልዕክተኛው በጌቴሴማኒ ለሞት ተላልፎ ሊሰጥም ሲል ሆነ በቤተልሄም ሲወለድ አልያም ከቤተልሔም በፊት በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ የራሱ የሆነ ፈቃድ ያለው የሥላሴ ሁለተኛ አካል ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ወደ ታች በወረደበት ደራጃ ልክ ሁሉ ፈቃዱን ለአብ አስገዛ እንጂ ያለ አማራጭ የቀረ አምላክ አልነበረም፡፡

 

ፈቃድ ያለ አማራጭ ትርጉም የለውም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ፈቃዱን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት (በራሱ ነፃ ፈቃድ) ሊጠቀም የሚችለው አማራጮች ሲኖሩት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክም ክርስቶስ ያለ አማራጭ ይሆን ዘንድ ግድ አላለውም፡፡ ይልቅስ ሕይወቱን በራሱ ፈቃድ እንዲሰጥ እንጂ ከእርሱ ማንም እንዳይወስዳት አሳልፎ ለመስጠትም ሆነ ለማስነሳት ስልጣን እንዲኖረው ትዕዛዝን ሰጠ (ዩሐ 10፡18) ፡፡

ግን ደግሞ መልዕክተኛው አማራጭ ከነበረው ምን አይነት አማራጭ ነበረው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ በጌቴሴማኒው የጭንቅ ጊዜ በእርግጥ ክርስቶስ አማራጭ ከነበረው ‹‹የተገለፀ አማራጭ አለ ወይ?›› ብሎ መጠየቅ አያስቀጣም፡፡ ክርስቶስ እንደ እውነተኛ አምላክ እና እውነተኛ ሰውነቱ በእርግጥ የማንም ጣልቃገብነት የሌለበት ነፃ ፈቃድ አለው፡፡ በዚያ በጌቴሴማኒ የጭንቅ ሰአት የነበረውን የአማራጭ ዝርዝር ባያሳየንም ነገር ግን ከፀሎቱ አንድ ነገር ማስተዋል እንችላለን፡፡

‹‹አባ ፤ አባት ሆይ ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው ፤ ነገር ግን የእኔ ቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን›› (ማር 14፡36)


በዚህ ፀሎት መሰረት መልዕክተኛው ክርስቶስ ‹‹ጽዋውን የማራቅ›› አማራጭ ነበረው ማለት ነው፡፡ ይህ ልናስተውለው የሚገባ ትልቅ እውነታ ነው፡፡ ክርስቶስ አማራጭ ስላጣ ወይንም አንዳንዶች እንደሚያስቡት ስለተገደደ አይደለም መልዕክተኛ የሆነው ደግሞም ስለ እኛ የሞተው ነገር ግን አማራጭ እያለ ያውም ፍትሃዊ አማራጭ እያለው ነው ‹‹የአንተ ፈቃድ ይሁን!›› ብሎ ጎልጎታን የመረጠው፡፡

ክርስቶስ አማራጭ እንደነበረው የምናስተውልበት ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከጌቴሴማኒ ብዙም ሳይርቁ አሳልፎ የሚሰጠው መንገድ ላይ እንደሆነ ገልጾላቸው ሳለ ጉዞ ከጀመሩ በኋላ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ ከካህናት አለቆች ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ዘንድ የተላኩ ሰይፍና ዱላ ከያዙ ብዙ ሰዎች ጋር አብሮ መጣ፡፡ ኢየሱስን ያዙት ፤ አሰሩት፡፡ ታዲያ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ፣ ሰይፉን መዝዞ በመሰንዘር የሊቀ ካህናቱን ጆሮውን ቆረጠው፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስ እንዲህ ይተርከዋል፡-


‹‹በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ቀርበው ኢየሱስን ያዙት፤ አሰሩትም፡፡ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ ፤ ሰይፉን መዝዞ በመሰንዘር የሊቀካህናቱን አገልጋይ ጆሮውን ቆረጠው፡፡ ኢየሱስም እንዲህ ሲል አለው ‹በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ፡፡ ካስፈለገ አባቴን ብጠይቀው ከዐስራ ሁለት ክፍለ ሰራዊት የሚበልጡ መላዕክት የማይሰድልኝ ይመስልሃልን? ይህ ቢሆን ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት ይሆናል ያሉት ነገር እንዴት ይፈጸማል? › ›› (ማቴዎስ 26፡50-54)

መልዕክተኛው ጌታ ኢየሱስ የተናረውን ልብ ካልን ‹‹ተገድጄ ፣ አማራጭ አጥቼ አልያም የሚዋጋልኝን አጥቼ የምሞት መሰለህን?›› የሚል አይነት ትርጉም ያለው ይመስላል፡፡ ጌታ ኢየሱስ በእርግጥ ከሰማይ የዐስራ ሁለት ክፍል ሰራዊት የሚበልጡ መላእክትን የማዘዝ አማራጭ ነበረው፡፡ ነገር ግን አማራጮቹን አልፈለጋቸውም፡ ለምን? ቢባል ቅዱሳት መፀሐፍት ይሆናል ያሉት እንዲፈም ነው (ቁ. 54) ፡፡

እዚህ ጋር ልናስተውለው የሚገባን ሌላኛው ነገር በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ በእርግጥ የሰውን ልጅ ለማዳን ወይንም ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ክርስቶስ በቅዱሳት መፅሐፍ ከተፃፈው ወጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ነው፡፡ የእግዚአብሔር የማዳን መንገዱ ይህ ነበር፡፡ ይህንን መንገድ ደግሞ ክርስቶስ በፈቃዱ መምረጥ ነበረበት፡፡ ቅዱሳት መፅሐፍት ያሉትን በመፈጸም ብቻ የእግዚአብሔርን ማዳን እቅድ ሊያሳካ እንደሚችል ክርስቶስ ተገንዝቧል፡፡ ስለዚህ መልዕክተኛው የራሱን አማራጮች ትቶ በቅዱሳት መጻሐፍት የተጻፈውን መፈጸም መርጧል፡፡

መልዕክተኛው በገዛ ፈቃዱ ራሱን ለአብ ፈቃድ በማስገዛት ቅዱሳት መጸሐፍ የሚሉትን ለመተግበር ወስኗል ማለት ነው፡፡ ያለ አማራጭ አልነበረም - ነገር ግን አማራጮቹን ትቶ ብቸኛውን የሰው ልጆችን የማዳንን መንገድ መረጠ፡፡ ለምን? ስለ እርሱ የተፃፈው እንዲፈጸም፡፡

አማራጭ ነበረው ፡፡  ‹‹ከአስራ ሁለት ክፍል ሰራዊት የሚበልጡ መላዕክትን›› ማዘዝ መብቱ! ነገር ግን ስለ እርሱ የተፃፈው እንዲፈፀም ‹‹የአንተ ፈቃድ ይሁን!›› ብሎ ስለ እኛ መሞትን መረጠ፡፡ ለምን? በቅዱሳት መፀሐፍ ስለ እርሱ የተፃፈው እንዲፈፀም!

በእርግጥ መፀሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ስለእኛ የተፃፈው እንዲፈጸም ቅዱሳን አማራጮቻችንን ሁሉ ትተን ‹‹የአንተ ቃድ ይሁን! ›› ማለት አለብን፡፡ ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ›› (ዩሐ 16፡33) ደግሞም ‹‹በእርግጥ በክርስቶስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ›› (2ኛ ጢሞ 3፡12) የሚሉትን ቃላትን ዘንግቶ (አልያም ሰርዞ) መከራን እንደክፉ ጠላት በማየት በተዋጠ ትውልድ መሃል የመከራ ምክንያት የሆኑብን ሰዎች አልያም ነገሮች (ተፈጥሮንም ጨምሮ) ላይ ከዐስራ ሁለት ክፍል ሰራዊት የሚበልጡ መላዕከት እንዲሰደዱልን የማንማፀን ስንቶቻችን ነን? ስለ እኛ የተፃፈው ይፈፀም ዘንድ ‹‹የአንተ ፍቃድ ይሁን!›› ማለት ይሁንልን!

መልዕክተኛው ከመሞት ይልቅ ከዐስራ ሁለት ክፍል ሰራዊት የሚበልጡ መላዕክት እንዲሰደዱለት አማራጭ ወስዶ ቢሆን ኖሮ ዕዳችን ባልተከፈለ ነበር፡፡ አንዳንድ የመከራ ጥሪዎች የትኛውም ያህል የሰማይ ሰራዊት ቢመጣ ቤተ ክርስቲያንን ተክቶ መጎንጨት የማይችለው ነው፡፡ ቢሆንም ግን ፍሬው ለብዙዎች እረፍት እና ደስታ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገዛ ፍቃዱን ለአብ አስገዝቶ ጎልጎታን በመምረጡ ብዙዎች በስሙ አምነው መዳን ችለዋል ደግሞም ከሐጢአት እና ከሰይጣን እስራት ነጻ ወጥተዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ በየፀሎት ማህበሮቻችን ላይ የተቃውሞው ፀሎት መስመር ለቆ አስተውላለሁ፡፡ የምንቃወመውን መቃወም መልካም ነው፡፡ የማንቃወመውን መጋፈጥ ግን ሊዘነጋ የማይገባው ነው፡፡ እዚህ ጋር አንዳንተላለፍ! እኔ ሁሉም የውጊያ ፀሎቶች ትክክል አይደሉም እያልሁ አይደለም፡፡ ነገር ግን አንዳንዱ ፀሎት ያልተፃፈልንን ከማንበብ የመነጨ አልያም የተፃፈልንን ከመሸሽ አንፃር የተመረጠ ሳይሆን አይቀርም፡፡

በሁሉም አንፃር የመከራ ምንጮች ብለን ባሰብናቸው ሁሉ ላይ ዘመቻ ከፍተን አንድጊዜ ዐስራ ሁለት ሺህ ሌላ ጊዜ ከዚያም በላይ የመላዕክት ሰራዊትን ስናዘምት የምንከርም ይመስለኛል፡፡ ግን ይህ ሁሉ ለምን? ለምን ‹‹ስስ›› ሆንን? ለምን የእኛ ጌቴሴማኒ የመጨረሻው ዘመን ላይ ቆመን ‹‹የአንተ ፈቃድ ይሁን!›› ብለን ከመፀለይና በፅናት ወንጌሉን ለማወጅ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ‹‹የአስራ ሁለት ክፍል ሰራዊት የሚበልጡ መላእክትን አዘዝሁበት!›› ለምን እንላለን? በድጋሜ ላስታውስ… የምንቃወማቸው ነገሮች የሉም አላልኩም! ነገር ግን በመከራ ውስጥ ያለን ፅናት ሲፈተሸ ከፀሎቶቻችን አብዛኞቹ የፍርሃት እና የሽሽት ናቸው፡፡ እንዲህ ሆነን ታዲያ ጌቴሴማኒ ላይ አለን፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ በጌታ ኢየሱስ ሕይወት ብንቀና አይፈረድብንም፡፡ እንዴት መስቀሉን ቻለው? እንዴት ጎልጎታን መረጠ? ምን አቅም ሰጠው? ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው ምክንያቱም የእምነታችን ጀማሪ እና ፈፃሚን እንድንመለከት ስለታዘዝን፡፡ (ዕብ 12፡2-3)

...

ማስታወሻ

የናኦል በፍቃዱ ‹‹አባት ሆይ … የአንተ ፈቃድ ይሁን›› የተሰኘው መጽሐፍ የፊታችን ጥቅምት 11 ቀን ተመርቆ ለንባብ ገበያ ላይ ውሏል። አዲሱ መጽሐፍ ከላይ የተገለጸውን መነሻ ሃሳብ ጨምሮ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ የመልዕክተኝነት ሕይወት የሚያትት ይሆናል፡፡

Pin It

Comments powered by CComment