ለክርስቲያን | ክርስቲያናዊ ሕይወት (በናኦል በፍቃዱ)

ቤንጃሚን ዲ. ውድ (Benjamin D. Wood) ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ በመማር እና ማስተማር ስርዓት ሂደት ውስጥ የተማሪዎችን እውቀት ለመመዘን የምርጫ ጥያቄዎች እንዲካተቱ ያደረጉት፡፡ የምርጫ ጥያቄ (Multiple Choice) ውስጥ ጥያቄ እና ለጥያቄው ደግሞ 4 ወይም 5 አማራጭ መልሶች ሲቀርቡ ከ4 ወይም 5ቱ ምርጫዎች አንዱ ብቻ ትክክለኛ መልስ ይሆናል፡፡

በዚህ ሂደት ተማሪውም ይህንን መልስ መለየቱ (መምረጡ) በጉዳዩ ላይ ዕውቀት እንዳለው ማሳየቱ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹ አማራጮች ሳይዘናጋ ትክክለኛውን ወደ መምረጥ ብስለት እንዳደገ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል:: ብልጥ መምህር ግን በምርጫው መልስ ብቻ አይረካም፡፡ ይልቅስ ‹‹ለምን እንዲህ መረጥክ/ሽ?›› ብሎ ተማሪውን ይጠይቃል፡፡ በዕወቀት እና በዕድል የመለሰ የሚለያዩት እንግዲህ የዚያኔ ነው፡፡

በተደጋጋሚ የምንሰማው ‹‹ሕይወት በብዙ ምርጫዎች የተሞላች ነች›› የሚለው አባባል እውነት ነው፡፡ ሰዎች በሕይወት አማራጮች እንደ ፈተና ምርጫ ጥያቄዎች ትክክለኛውን እና ትክክለኛ ያልሆነውን በመለየት መወሰን ይኖርብናል፡፡ እንደ ክርስቲያን ክርስቶስን ለመከተል የወሰንኩት ውሳኔ እጅግ ትክክለኛ እና አስፈላጊ ውሳኔ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ክርስቲያኖች ክርስትናን ለመቀበል እና የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን የወሰነው ውሳኔ ትክክለኛው ውሳኔያችን ነው፡፡

ታዲያ ክርስቶስን ስንቀበል ሊያዘናጉን ከመጡ ከሌሎች አማራጮች መካከል ለይተን እንደሆነ እንደመረጥን የታወቀ ነው፡፡ በምድር ላይ ብዙ ሃይማኖቶች ፣ አስተሳሰቦች ፣ ፍልስፍናዎች እና ብዙ ተከታዮች ያሏቸው ሰዎች አሉ፡፡ እኛ ግን ‹ክርስቶስን ይሻለናል ፤ እርሱ ትክክል ነው› ብለን መርጠናል፡፡ ተከታዩ የብልጡ መምህር ጥያቄ ታዲያ ለምን? የሚለው ነው፡፡ ለምን ኢየሱስን መረጥን? ለምን ጌታ ይሻላል አልን? ለምን ወንጌሉ ትክክል ነው ብለን አመንን? ለምን ኢየሱስ?

ለዚህ ጥያቄ እጅግ ብዙ መልሶች ቢኖሩኝም፡፡ ‹ሌሎች አማራጮችን ትቼ ለምን ኢየሱስን ተከተልሁ?› ብዬ ስጠይቅ ከሚመጡልኝ ብዙ መልሶች ውስጥ ዋና ዋና የሆኑትን አምስቱን ብቻ በቀጣይ ላስነብባችሁ፡፡

ኢየሱስ… ምክንያቱም…

 1. ትንሳኤው፡-

ኢየሱስ እርሱ ‹‹ጌታዬ ፤ አምላኬም›› (ዩሐ 20፡20) ነው ብዬ እንደ ሐዋርያው ቶማስ አምኜ እንድከተለው ካደረጉኝ ምክንያቶች ሁሉ ቀዳሚው ምክንያት የክርስቶስ ኢየሱስ ከሞት መነሳት እውነታነት ነው፡፡ ከነበሩት አማራጮች ሁሉ ኢየሱስን (እና ክርስትና እምነትን) የሚለየው ዋነኛው ምክንያት ይህ ነው፡፡ ሌሎች አማራጮች ብለን የምናያቸው የ ትልልቅ ሃይማኖት መሪዎች እና መስራቾች ፣ ታላላቅ ፈላስፋዎች እና የጦር መሪዎች በመሉ ሞተዋል፡፡ ሞተው ቀርተዋል፡፡ ከሞት ስለመነሳታቸውም ሆነ ‹ከሞት እነሳለሁ› ብለው ስለመሞታቸው ታሪክ ምንም አያወራም፡፡ ተከታዮቻቸውም ይህንን አያወሩም፡፡ የኢየሱስ ግን ይለያል፡፡ ከመሞቱ በፊት አስቀድሞ ‹ከሞት እነሳለሁ› ብሎ ነበር (ማቴ 16፡21) ፡፡ ማንም ሊተርፍበት በማይችልበት አሰቃቂ የመስቀል ሞት ሞተ! ስለሞቱም ክርስቲያን ያልነበሩ ጸሐፊያን እንኳ መሰከሩለት፡፡ በመቀጠልም ተከታዮቹ ከሞት ተነስቶ እንዳዩት በአደባባይ መሰከሩ፡፡ ስለምስክርነታቸውም ብዙ ዋጋ ከፈሉ፡፡ ይህም ሳይበቃ እንደ ተርሴሱ ሳውል (ኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ የሆነው) ያሉ አሳዳጆቹን እንኳ ሳይቀር ይህ እውነት ማረካቸው፡፡ ለምን ኢየሱስ? ምክንያቱም እርሱ ብቻ ከሞት ስለተነሳ!

 1. ሞቱ ፡-

ሌላኛው ኢየሱስን የተቀበልኩበት ትልቁ ምክንያት የኢየሱስ ሞት ነው፡፡ የኢየሱስን ሞት ከሌላው የሃይማኖት መሪ ሞት ምን ይለየዋል? ለዚህ ሶስት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

 1. የኢየሱስ ሞት ድንገተኛ አለመሆኑ፡- ኢየሱስ ሞቱን እና አሟሟቱን አስቀድሞ ደጋግሞ ይናገር ነበር (ማቴ 8፡31-38 ፣ 16፡21 ፣ ሉቃ 18፡31-33) ፡፡ ኢየሱስ በድንገተኛ አደጋ ወይንም በተፈጥሮ አይደለም የሞተው፡፡ በታሰበበት እና በታቀደበት ሞት ነበር የሞተው፡፡ ሌሎች አማራጮቻችንን ስናይ ግን ሁሉም የሞቱት በድንገተኛ ምክንያቶች (እንደ ጦርነት እና የተፈጥሮ አደጋ) አልያም በአድሜ ብዛት ነው፡፡
 2. የኢየሱስ ሞት የክርስትና መነሻ ምክንያት አለመሆኑ፡- ክርስትና የኢየሱስ የሰማዕትነት ገድል አይደለም፡፡ የኢየሱስ ሞት እንደውም ተከታዮቹቱን በታትኗቸው እና ተስፋ አስቆርጧቸው ነበር፡፡ የኢየሱስ ሞት ከገድልነት ያለፈ ትርጉም ያለውም ለዚህ ነው፡፡
 3. በሞቱ ያስተላለፈው ምክንያት ልዩ መሆኑ፡- ሁሉንም የሃይማኖት መሪዎች ሞት ስንመለከት ከሞታቸው ጀርባው የሆነ ምክንያት አለ፡፡ ከኢየሱስ ንግግርም ሆነ ከአሟሟቱ ሁኔታ እንደምረዳው በሞቱ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልዕክት ልዩ እንደሆነ ነው፡፡ ኢየሱስ በሞት የእግዚአብሔር ፍቅርን (ዩሐ 3፡16) ፣ መስዋዕትነትንና (ዩሐ 15፡13) እና እስከመጨረሻው መውደድን (ዩሐ 13፡1) ሰብኳል፡፡
 1. ውልደቱ ፡-

የኢየሱስ መወለድ ሌላኛው ኢየሱስን እንድቀበለው የሚያደርገኝ ትልቁ ምክንያት ነው፡፡ ኢየሱስ የሚጸነስበት ሁኔታ (ኢሳ 7፡14) እና የሚወለድበት ቦታ (ሚኪ 5፡2) እርሱ ከመወለዱ ከብዙ መቶ አመታት በፊት የተተነበየለት በታሪክ ብቸኛው ሰው ነበር፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የኢየሱስ መወለድ በራሱ በጊዜው የነበሩትን ነገስታትን ያስጨነቀ እና ያሳወከ ጉዳይ ነበር፡፡ ክርስቲያኖች ኢየሱስ አምላክ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህ አንደኛው ማስረጃ ደግሞ ውልደቱ ነው፡፡ በነብያቱ አምላክ እንደሚመጣ ተነገረ (ኢሳ 40፡3)፡፡ ይኸው ትንቢት በክርስቶስ ውልደት እንደተፈጸመ ተበሰረ (ማቴ 4)፡፡ የኢየሱስ ውልደት አምላክ ሰው የሆነበት ፤ ቃል ስጋ የለበሰበት ለመሆኑ ሐዋርያቱም መስክረዋል፡፡

 1. ሕይወቱ ፡-

የኢየሱስ ሕይወት ኢየሱስን እንድመርጥ ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ ኢየሱስ አስተምህሮ ፣ ድርጊቶች እና የአኗኗር ዘይቤ በምድር ላይ ከኖሩት ሌሎች አማራጮቻችን ሁሉ ልዩ ግብረገባዊ ስብዕናን ያላብሰዋል፡፡ የኢየሱስ አስተምህሮ ፍቅርን መሰረት ያደረገ ነበር፡፡ የኢየሱስ ድርጊትም ከፍቅር የመነጨ ነበር፡፡ የአኗኗር ዘይቤውም ግለኝነት ፣ የእኔነት ስሜት እና የስልጣን ጥማት የሚታይበት አልነበረም፡፡ ይልቅስ ከሁሉ ተሸሽጎ ፣ ለሁሉ የኖረ ነበር፡፡ ፍቅርን ሰብኮ ፣ ፍቅርን የኖረ ነበር፡፡ ይህንን ለመመስከር ደግሞ ክርስቲያን መሆን አይጠበቅበትም፡፡ በክርስቶስ ያላመኑ ብዙ ሰዎች ይህንን መስክረዋል፡፡ ፈረንሳያዊው የጦር መሪ ናፖሊዩን ቦናባርቴ በአንድ ወቅት ስለክርስቶስ ሲናገር ‹‹በታላቁ ስክንድሮስ ፣ ቄሳር ፣ ቻርላማኝ እና እኔ ትላልቅ መንግስታትን መስርተናል፡፡ የእኛ ክህሎት ግን በምን ላይ ነበር የተመሰረተው? በሃይል ላይ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መንግስቱን በፍቅር ላይ መሰረተ ፤ በዚህ ሰዓት ሚልዮኖች ስለስሙ ይሞቱለታል!›› ብሏል፡፡ ለምን ኢየሱስ? አስተምህሮው ፣ ድርጊቱ እና አኗኗሩ ፍቅርን መሰረት ያደረገ ስለነበር፡፡

 1. ሕይወቴ ፡-

በመጨረሻም የግል ሕይወቴ ትልቁን መልስ ይሰጠኛል፡፡ ‹‹ኢየሱስን ካገኘሁ በኋላ ተለውጫለሁ›› በማለት ልደመድም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሰው ገንዘብ ወይም ትዳር ካገኘ በኋላም ይለወጣል፡፡ ኢየሱስን ካገኘሁ በኋላ ሕይወቴ ፍጹም ተቀይሮ ስህተት የማልሰራ ሰው ሆኛለሁ ብዬም አልዋሽም፡፡ ነገር ግን ኢየሱስን ከመረጥሁ በኋላ ሐይወቴ እንደተቀየረ ይሰማኛል፡፡ ‹ኢየሱስ ሕይወቴን ቀይሮታል› ስል ከሞት የተነሳው እግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደግል አዳኜ አድርጌ ከተቀበልሁ በኋላ የሚከተሉት አራት ነገሮች በዋነነት በሕይወቴ ተቀይረዋል ማለቴ ነው፡፡

 • ስለሞት ያለኝ አመለካከት ተቀይሯል፡፡ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱ ለእኔ ትልቅ ተስፋ ሆኖኛል፡፡ ሞት መጨረሻዬ ደግሞም ማብቂያዬ አይደለም፡፡ ከሞት በኋላም ጥፋት ይመጣብኛል ብዬ አልሰጋም፡፡ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱ ለሐዋርያቱ ትንሳኤን ተስፋ እንደሰጠ (1ኛ ጴጥ 1፡2)እኔም የትንሳኤን ተስፋን ሰጥቶኛል፡፡ የሞት ፍርሃት ከእኔ ላይ ተነስቷል፡፡ ኢየሱስ ለሚያምኑት በሰማይ ቤት እንዳዘጋጀ (ዩሐ 14፡3) አምኛለሁ፡፡ ከዚህም የተነሳ በዚህ አስጨናዊ አለም ሰላም ይሰማኛል፡፡
 • ስለ ሕይወት ያለኝ አመለካከት ተቀይሯል፡፡ ኢየሱስ ስለ ሕይወት የነበረኝን የተሳሳተ ግንዛቤ ቀይሮታል፡፡ ሕይወት - ጊዜያዊ ፣ ከንቱ እና ትርጉም የለሽ ከነበረችበት አስተሳሰብ አውጥቶ ሕይወት ምንም እንም እንኳ በዚህ ምድር ቆይታ ጊዜያዊ ብትሆንም ነገር ግን ውድ እና በክርስቶስ ደግሞ ትርጉም ያላት መሆኗን ወደ ማወቅ አምጥቶኛል፡፡ ሕይወቴን ትርጉም በማይሰጡ ነገሮች ላይ ከማዋል ትርጉም ወዳላቸው ነገሮች እንዳዞር ኢየሱስ ረድቶኛል፡፡ ሐጢአት ፣ ሱስ እና ለስጋ ደስታ ብቻ የሚደረጉ ነገሮች ዘላለማዊ ፋይዳ እንደሌላቸው አስገንዝቦኛል፡፡ ይልቅስ እግዚአብሔርን መውደድ እና መታዘዝ የደስታዎች ሁሉ ጥግ ምንጭ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ስለዚህም የሕይወት አላማ እግዚአብሔርን መውደድ እና መታዘዝ ብሎም በዚያ ውስጥ ያለውን ደስታ ማጣጣም ብዬ ተርጉሜዋለሁ፡፡
 • ስለ ራሴ ያለኝ አመለካከት ተቀይሯል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ካመንሁ ወዲህ ስለራሴ ያለን አመለካከት ተቀይሯል፡፡ ይህም ተስፋ የሌለኝ እና ለምንም የማልሆነ ሰው አድርጌ ራሴን ከመቁጠር በእርሱ በኩል ከእግዚአብሔር ባገኘሁት ምህረት ራሴን ይቅር ማለት ችያለሁ፡፡ መለወጥ እንደሚቻል በክርስቶስ ተስፋ አግኝቻለሁ፡፡ ዛሬም ድረስ ለውጡ አላበቃም፡፡ በየዕለቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየተማርሁ ለመለወጥ የእርሱን እገዛ እጠይቃለሁ፡፡ ይህም የሆነው ጌታ ኢየሱስ ራሴን ይቅር እንድል ስላስቻለኝ ነው፡፡
 • ስለ ሰዎች ያለኝ አመለካከት ተቀይሯል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር ስብከት ራሴን ይቅር እንድል ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ያውም ለሚጠሉኝም በጎ እይታ እንዲኖረኝ እና በፍቅር እንዳያቸው አድርገጎኛል፡፡ ኢየሱስ ሰዎችን እንድወድ ትምህርት እና አቅም ሰጥቶኛል፡፡ በወንድሜም በጠላቴም ላይ ጦር እንዳላነሳ ይልቅስ በፍቅር እንድሸነፍ አስተምሮኛል፡፡ ይህ ፍቅር ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ በየጊዜው እየተማርሁት ቢሆንም ዛሬም ይሄን ለውጥ በሕይወቴ እያየሁ እንደሆነ ግን አልክድም፡፡

ለምን ኢየሱስ? ከሞት ስለተነሳ! ለምን ኢየሱስ? ስለ እውነተኛ ፍቅር ስለሞተ! ለምን ኢየሱስ? በትንቢት ስለተወለደ! ለምን ኢየሱስ? የፍቅር አስተምህሮው ፣ ድርጊቱ እና አኗኗሩ ፍጹም ስለሚጣጣም! ለምን ኢየሱስ? ሕይወቴን ስለቀየረ!

Pin It

Comments powered by CComment